****የእኛው ጠማማ ነው!****
ከእለታት አንድ ቀን ዛፎች ተሰባስበው
በአንድነት በህብረት ጉባኤ አዘጋጅተው
ማነው የሚቆርጠን እያሉ ሲመክሩ
የመፍትሄ ሃሳብ ሁሉን ሲቆፍሩ
ሃሳብ እያወጡ ነገሩን ሲያጣሩ
አንዱ ተነሳና ነገሩ የቆጨው ልቡ ያረረበት
ንግግር ጀመረ እንዲህ በማለት
ከዛሬ  በፊት ስሜን ለማታውቁኝ
አሁን ልንገራችሁ “ዋርካ” እባላለሁኝ
ከዚህ በመቀጠል በእግዚአብሔር ሰላምታ ሰላም እያልኩኝ
እኔ የማውቀውን እናገራለሁኝ
እኔ አካሌ ግዙፍ ታላቅ ሆኖ ሳለ
በእሳት በመዶሻ በደምብ የተሳለ
ቆርጦ የሚጥለኝ አንድ መጥረቢያ አለ
ብሎ በጉባኤው ቆሞ ተናገረ
ከዚህ በመቀጠል ሌላው ተነሳና
ስሙን “ግራር” ብሎ አስተዋወቀና
ነገሩን ቀጠለ በውስጡ ያለውን
አየቆራረጠ  ያስቸገረውን
“እኔ  አካሌ ሁሉ እሾህ የከበበኝ
ዘወትር የሚጠብቀኝ ማንም እንዳይነካኝ
በዚህች ምድር ላይ የተከበርሁ ነኝ!!!”
ነገር ግን ወንድሞች እሾሁን ሳይፈራ
አኔ ማን እንደሆንኩ ቀርቦ ሳያጣራ
ዘወትር የሚቆርጠኝን  ማነው ስል ስጠይቅ
ግራ በመጋባት ሁልጊዜ ስጨነቅ
በራሴ ጥያቄ ከራሴ ስዳረቅ
አሁን ግን አወቅሁት ነገሩን መርምሬ
ሳልደቅም ሳልታክት ሜዳውን ሁል ዞሬ
ከዚህ ከጉባኤው መጥቻለሁ ዛሬ
ወንድሞቼ አዳምጡኝ ልናገር ዘርዝሬ
“እኔ አንደምመስለኝ ሲጣራ ነገሩ
በፍጹም “አትሙ” ሌላ አትጠርጥሩ
እኛን የሚቆርጠን አይደለም መጥረቢያው አይደለም ምሳሩ
የእኛው ጠማማ ነው አትጠራጠሩ”
ብሎ ተናገረ ግራሩ ቆጭቶት
የወንድሞቹ ነገር በጣም ግራ ገብቶት
ይህንን ተናግሮ ግራር አረፍ ሲል
አንደበተ ችኩል ተነስቶ አንድ ቀላል
“ወንድሞቼ ስሜ “ቀርቀሃ” ይባላል
ወንድሜ አቶ ግራር አንደተናገረው
እኛን የሚቆርጠን የእኛው ጠማማ ነው
ግን እርምጃውን ምን እንውሰድበት
ምንስ እናድርገው ምን  እንፍረድበት
አለና ቀርቀሃ በችኩል  አንደበት
በታዳሚው መሃል ሞት ይፈረድበት
ብሎ አረፍ ሲል  ቶሎ በዚያች ቅጽበት
ሌላ “ባህርዛፍ” የሚባል ቀርቀሃ አስገርሞት
ብድግ አለና ከተቀመጠበት
“ዛሬ ምግባር ጎድሎት እኛን ቢያስቆርጠን
ለምን ሞት እንፍረድ በእኛ በወንድማችን
እንዲህ የጭካኔ የሞት ውሳኔ ቃል
ወንድሜ ቀርቀሃ ከአንተ እንዴት ይወጣል ???
ያም ሆነ ይህም ሆነ ነገሬን ላጠቃል
ቶሎ እንለያይ ጊዜውም መሽቷል
አለና ባህር ዛፍ  በዚያው በጉባዔው
እንደ እኔ ሃሳብ እኔ አንደማስበው
ከመግደል ይልቁንስ ወንድማችንን እንምከረው
በአንድ ተሰባስበን በግልጽ እንገስጸው  
የፈጣሪ  ነገር ምኑ ይታወቃል ??
ተስፋ ካልቆረጥን ደግሞም ይመለሳል
ምክር እንኳን የእኛን ልጅ ባዕድ ያፋቅራል   
አሁን----------
ሰዓት ስለመሸ ቶሎ ከቤት እንግባ
በማለት በአንድነት ጉባኤው አለቀ በደማቅ ጭብጨባ !!!!!!

*************አንሙት አለሙ*********    

Comments

Popular Posts