>>>>>ይቅር አልመረቅ!!!<<<<<              
      (16/02/2010 አ-ም)
ስማኝማ መንግስት!!
ሳትቸኩል በትዕግስት
ይሄን አለኝ ብለህ ላትነካ ጫፌን ላትቆርጥ ከደሞዜ
ግባና ቃልኪዳን ግባና ኑዛዜ
ልብ ከጆሮ አርገህ ስማኝማ አንድ ጊዜ
የምነግርህ አለኝ ቁርጥ ሆኗል ዛሬ
ይኸው እንደምታየኝ ከጠዋት እስከ ማታ ከማስታወቂያ ቦርድ  ከዚህ ተገትሬ
የፊቴ ፀዳሉ እንዳልሆነ  ሆኖ ከስቼ ጠቁሬ
ሥራ አጥ እቆጥራለሁ
የወደፊት ህልሜን በቀጨጨ ተስፋ አሻግሬ አያለሁ
የማይሆን ጥያቄ ያውም ማይመለስ አወጣ አወርዳለሁ
በተወልድኩባት ባደግኩባት ምድር
ገና ሳልመረቅ ኮስትሸር በሚሉት ጠልቄ በብድር
ስለ እሱ አስባለሁ!
ስለ ቀጣይ ህልሜ ስለ ወደፊቱ ስለ እኔ አስባለሁ
ስለ እናት አባቴ እኔን ለማስተማር ባጭር ለታጠቁ
ስለ እህት ወንድሜ የኔን እርዳታ ለሚጠባበቁ
ዲግሪ ተሸክመው ዶክመንት ተሸክመው  በሥራ ፍለጋ ዓመት ሁለት ዓመት ደክመው ለወደቁ
በሕዝብ ተመርጠው በብልሹ አሰራር በሙስና ቅሌት ለተጨማለቁ
በየአደባባዩ በፌደራል ፖሊስ በክርን ለተደቁ
ስለ እነዚህ ሁሉ በውስጤ አስባለሁ
ደግሜ እንደገና የወደፊት ሕልሜን አወጣ አወርዳለሁ
ታዲያ እንዴት ይሻላል?
ይሄን ሁሉ ነገር ሳይለማኝ አስቤ
ራሴ ሰው ሳልሆን፣እናት አባት ሳልጦር፣ሐገሬን ሳልረዳ በጭንቅ ተከብቤ
በአንድ ጊዜ በአንድ አፍታ ፀጥ  ትበል ልቤ?!!!
ስማኝማ መንግስት-----
ዘወትር እንደማየው በየመስሪያ ቤቱ
ቁጥሩ *ማይታወቅ ብዙ ሺ ምሩቃን ዶክመንት ተሸክሞ በሥራ ፍለጋ የጠቆረ ፊቱ
ሳያቸው አዝናለሁ!
ደግሞ እገረማለሁ!
ደግሜ እንደገና ጥያቄ አወርዳለሁ ጥያቄ አወርዳለሁ
ልጠይቅ እልና በፍርሃት በጭንቀት ምላሴን ጎርሳለሁ
ዝምታ ወርቅ ነው በሚል አጉል ብሂል ራሴን ገዛለሁ
ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ነሸጥ ሲያደርገኝ እንዲህ እፅፋለሁ
*************************
ስማኝማ መንግስት!
ሳትቸኩል በትዕግስት
ይሄን አለ ብለህ  ላትነካ ጫፌን ላትቆርጥ ከደሞዜ
ግባና ቃል ኪዳን ግባና ኑዛዜ
ልብ ከጆሮ አርገህ ስማኝማ አንድዜ
ቀጣይ ለወደፊት የስራ አጥን ቁጥር በሩብ ለመቀነስ
የደሞዝን መጠን በእጥፍ ለማሳነስ
በጥሩ ስራችን ዉሃ ለመቸለስ
ድንጋይ የሚያነሳን በጥይት ለማቅመስ
የንፁሃንን ደም በከንቱ ለማፍሰስ
እስከ ዓለም ፍፃሜ ስልጣን ላይ ለመኖር
በእርጅና ዘመንህ አልጋ ላይ ለመጦር
አስበሃል አይደል?
ታዲያ ጥሩ ነዋ መኖር አራት ኪሎ
ወዲያው ከምርህ ነው የሆንክ ኬልኬሎ
ኧረ እንዲያው ምን ገዶኝ
ከአንተ ጋር ሳወራ እኔም የሆንኩ ነኝ !!
በቃ ይቅር በለኝ
********
ስማኝማ መንግስት---
ኑሮ ግን እንዴት ነው?
እውነቴን እኮ ነው!
አንተማ ታድለህ
በሄድክበት ሁሉ ጮቤ ትረግጣለህ
እውነቴን እኮ ነው!
የከተማ ቦታን በሊዝ እንደመያዝ
ታክስ ግብር እያሉ  ሕዝቡን እንደመግረዝ
ከአመት ሁለት ጊዜ ግብር እንደመሰብሰብ
ጥያቄ *ሚያነሳን በአግአዚ ወታደር ተግቶ እንደማስደብደብ
እነ ክልል አንድን እንደመንከባከብ
ምን መታደል አለ?
እውነቴን እኮ ነው!
በስተመጨረሻ የማሳስብዎ
አንድ ነገር አለኝ! ጆሮዎን ኮርኩረው ይስሙኝ እባክዎ
በሞቴ ና እና እየን ምን እንደምንበላ ምን እንደምንጠጣ
ምን እንደምናገኝ ምን እንደምናጣ
ምን እንደምን’ግድ ምን እንደምናተርፍ
ምን እንደምንከፍል ምን ለእኛ እንደሚተርፍ
የት እንደምናድር ምን እንደምንለብስ
በግፍ ስንበደል ማንን እንደምንከስ
በሞቴ አንድቀን ና
ካልቻልክ በባቡር ከቻልክ በመኪና
ዋ እንዳትቀር
እንዲህ አሞናሙነን ጠርተንህ በክብር
ወዲያው ልትመጣ ነው? የሆንህ እንከፍ ነገር!!!
**************************

Comments

Popular Posts